20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 1

የእስራኤል መንግሥትና የይሁዳ መንግሥት ሁለቱም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋርበሲና ተራራ ያደረገውን ቃልኪዳን አፈረሱ። እግዚአብሔርንስሐ እንዲገቡና እንደገና እንዲያመልኩት ሊያስጠነቅቃቸው ነቢያቱንላከ፣ እነርሱ ግን አንታዘዝም አሉ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 2

ስለዚህ እግዚአብሔር ጠላቶቻቸው እንዲያጠፉአቸው በመፍቀድ ሁለቱንም መንግሥታት ቀጣቸው። የኃያልዋ፣ የጨካኝዋ አገር የአሦር ንጉሠ ነገሥት ግዛት የእስራኤልን መንግሥት አጠፋች፣ ዋጋ ያለውን ነገር ሁሉ ወሰደች፣ ከአገሪቱ አብዛኛውንም አቃጠለች።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 3

አሦርያውያን መሪዎችን፣ ሀብታሞችን፣ እንዲሁም ሙያ የነበራቸውን ሰዎች ሁሉ ሰበሰቡና ወደ አሦር ወሰዱአቸው። ያልተገደሉት በጣም ድሆች የነበሩት እስራኤላውያን ብቻ በእስራኤል መንግሥት ቀሩ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 4

ከዚያም አሦራውያን የእስራኤል መንግሥት በነበረባት ምድር እንዲኖሩ ባዕዳንን አመጡ። ባዕዳኑ የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ሠሩና በዚያ ቀርተው የነበሩትን እስራኤላውያን አገቡ። ባዕዳንን ያገቡት የእስራኤላውያን ዝርያዎች ሳምራውያን ተብለው ይጠሩ ነበር።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 5

የእስራኤል መንግሥት ሕዝብ እግዚአብሔርን ስላላመኑበትና ስላልታዘዙት እንዴት እንደ ቀጣቸው በይሁዳ መንግሥት የነበሩት ሕዝብ ዐዩ። እንደዚያም ሆኖ ግን የይሁዳ መንግሥት ሕዝብ የከነዓናውያንን አማልክት ጨምሮ ጣዖታትን አመለኩ። እግዚአብሔርም እንዲያስጠነቅቁአቸው ነቢያትን ላከ፣ እነርሱ ግን አንሰማም አሉ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 6

አሦራውያን የእስራኤልን መንግሥት ካጠፉ ከ100 ዓመታት ገደማ በኋላ የይሁዳን መንግሥት እንዲወጉ እግዚአብሔር ባቢሎናውያንን ላከ። ባቢሎን ኃያል የንጉሠ ነገሥት ግዛት ነበረች። የይሁዳ ንጉሥ የናቡከደነፆር አገልጋይ ለመሆንና በያመቱ ብዙ ገንዘብ ሊከፍለው ተስማማ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 7

ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ የይሁዳ ንጉሥ በባቢሎን ላይ ዓመፀ። ስለዚህ ባቢሎናውያን ተመልሰው መጥተው የይሁዳን መንግሥት ወጉ። የኢየሩሳሌምን ከተማ ያዙ፣ ቤተ መቅደሱን አጠፉ፣ እንዲሁም የከተማይቱንና የቤተ መቅደሱን መዛግብት ሁሉ ወሰዱ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 8

የይሁዳ ንጉሥ ስላመፀበት ሊቀጣው የናቡከደነፆር ወታደሮች የይሁዳን ንጉሥ ወንድ ልጆች በፊቱ ገደሉ፤ እርሱንም ዓይኖቹን አሳወሩ። ከዚያ በኋላ በባቢሎን በእስር ቤት እንዲሞት ንጉሡን ወሰዱት።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 9

ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ በእርሻ እንዲሠሩ እጅግ በጣም ድሆች የሆኑትን ሰዎች ብቻ በመተው ከሞላ ጐደል የይሁዳን መንግሥት ሕዝብ ሁሉ ወደ ባቢሎን ማርከው ወሰዱ። የእግዚአብሔር ሕዝብ የተስፋዪቱን ምድር እንዲለቁ የተገደዱበት ይህ ወቅት ምርኮ ተብሎ ይጠራል።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 10

ምንም እንኳ እግዚአብሔር ወደ ምርኮ በመውሰድ ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ቢቀጣቸውም እነርሱንና ተስፋዎቹን አልረሳም። እግዚአብሔር ሕዝቡን መጠበቁንና በነቢያቱ በኩል እነርሱን ማነጋገሩን ቀጠለ። ከሰባ ዓመት በኋላ፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንደ ገና እንዲመለሱ ተስፋ ሰጠ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 11

ከሰባ ዓመታት ገደማ በኋላ፣ የፋርስ ንጉሥ ባቢሎንን አሸነፈ፣ ስለዚህ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት የባቢሎንን ንጉሠ ነገሥት ግዛት ተካ። አሁን እስራኤላውያን አይሁዶች ተብለው ተጠሩ አብዛኞቻቸውም ሕይወታቸውን በሙሉ በባቢሎን የኖሩ ነበሩ። በጣም ያረጁ ጥቂት አይሁዶች ብቻ የይሁዳን ምድር አስታወሱ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 12

የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ጠንካራ ነገር ግን ለያዛቸው ሕዝብ መሐሪ ነበር። ቂሮስ የፋርሳውያን ንጉሥ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ወደ ይሁዳ መመለስ የፈለገ ማንኛውም አይሁዳዊ ፋርስን ለቆ ወደ ይሁዳ መመለስ እንደሚችል ትእዛዝ ሰጠ። ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲሠሩ የገንዘብ ድጋፍ ሳይቀር አደረገላቸው! ስለዚህ በምርኮ ከቆዩባቸው ሰባ ዓመታት በኋላ፣ ጥቂት የአይሁዶች ቡድን በይሁዳ ወዳለችው ኢየሩሳሌም ከተማ ተመለሱ።

20. ምርኮና ከምርኮ መመለስ — illustration 13

ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ፣ ቤተ መቅደሱንና በከተማዪቱ ዙሪያ ያለውን ቅጥር እንደ ገና ሠሩ። ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ በሌሎች ሕዝቦች የተገዙ ቢሆኑም፣ ዳግመኛ በተስፋዪቱ ምድር ኖሩና በቤተ መቅደሱ አመለኩ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከ2ኛ ነገሥት 17፤ 24-25፤ 2ኛ ዜና 36፤ ዕዝራ 1-10፤ ነህምያ 1-13።

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).