45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 1

በጥንትዋ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት መሪዎች አንዱ እስጢፋኖስ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። እርሱ መልካም ስም ያለውና መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላበት ሰው ነበር። እስጢፋኖስ ብዙ ተአምራትን ያደረገና ሰዎች በኢየሱስ እንዲያምኑ አሳማኝ ምክንያት የሚያቀርብ ሰው ነበር።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 2

አንድ ቀን እስጢፋኖስ ስለ ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ፣ በኢየሱስ ያላመኑ አንዳንድ አይሁድ ከእስጢፋኖስ ጋር መከራከር ጀመሩ። በጣም ተቈጡና ስለ እስጢፋኖስ ለሃይማኖት መሪዎች ዋሽተው ተናገሩ። “ስለ ሙሴና ስለ እግዚአብሔር ክፉ ነገሮችን ሲናገር ሰምተነዋል!” አሉ። ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎቹ እስጢፋኖስን ያዙትና ተጨማሪ የሐሰት ምስክሮች ስለ እስጢፋኖስ ዋሽተው ወደተናገሩበት ወደ ሊቀ ካህናቱና ወደ ሌሎቹ የአይሁድ መሪዎች አመጡት።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 3

ሊቀ ካህናቱ እስጢፋኖስን፣ “እነዚህ ነገሮች እውነት ናቸውን?” ብሎ ጠየቀው። እስጢፋኖስ ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ዘመን ድረስ እግዚአብሔር ስላደረጋቸው ብዙ ታላላቅ ነገሮች፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ሕዝብ በተከታታይ በእርሱ ላይ ስለ ማመፃቸው በማስታወስ መልስ ሰጠ። ከዚያም እንዲህ አለ፣ “እናንተ አንገተ ደንዳኖችና ዓመፀኞች ሕዝብ ልክ ቅድማያቶቻችሁ እግዚአብሔርን እንደ ተቃወሙትና ነቢያቱን እንደ ገደሉ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ። እናንተ ግን ከእነርሱ ይልቅ የባሰ ነገር አድርጋችኋል። መሲሑን ገድላችኋል!”

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 4

የሃይማኖት መሪዎቹ ይህንን በሰሙ ጊዜ፣ ጆሮአቸውን እስኪደፍኑና ከፍ ባለ ድምፅ እስኪጮኹ ድረስ በጣም ተቈጡ። እስጢፋኖስን ከከተማይቱ ውጪ ጐተቱትና ሊገድሉት በድንጋይ ወገሩት።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 5

እስጢፋኖስ በመሞት ላይ እያለ፣ “ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበላት” ብሎ ጮኸ። ከዚያም በጉልበቱ ተንበረከከና፣ “ጌታ ሆይ፣ ይህንን ኃጢአት አትቊጠርባቸው” ብሎ እንደ ገና ጮኸ። ከዚያ በኋላ ሞተ።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 6

ሳውል የተባለ ወጣት እስጢፋኖስን ከገደሉት ሰዎች ጋር ተስማማና በእርሱ ላይ ድንጋይ በሚወረውሩበት ጊዜ ልብሳቸውን ይጠብቅ ነበር። በዚያን ዕለት በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙ ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች ማሳደድ ጀመሩ፣ ስለዚህ አማኞቹ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሸሹ። ነገር ግን ስደቱ ቢኖርም እንኳ፣ በሄዱበት ስፍራ ሁሉ ስለ ኢየሱስ ሰበኩ።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 7

ፊልጶስ የተባለ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር በስደቱ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ከሸሹት አማኞች አንዱ ነበር። ወደ ሰማርያ ሄዶ ስለ ኢየሱስ ሰበከና ብዙ ሰዎች ዳኑ። ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ በምድረ በዳ ወዳለ አንድ መንገድ እንዲሄድ ለፊልጶስ ነገረው። ፊልጶስ በመንገዱ በመሄድ ላይ እያለ አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን በሰረገላው ሲሄድ ዐየ። ወደዚህ ሰው ሄዶ እንዲያነጋግረው መንፈስ ቅዱስ ለፊልጶስ ነገረው።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 8

ፊልጶስ ወደ ሰረገለው በቀረበ ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊው ነቢዩ ኢሳይያስ ከጻፈው ውስጥ አንዱን ክፍል ሲያነብ ሰማ። ሰውዬው እንዲህ አነበበ፣ “እንደሚታረድ በግ ነዱት፣ በግ ዝም እንደሚል አንድም ቃል አልተናገረም። በፍርድ ተወሰደ፣ አላከበሩትምም። ከሕያዋን ምድር አስወገዱት።”

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 9

ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን፣ “የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ብሎ ጠየቀው። ኢትዮጵያዊው፣ “አይደለም። የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር ላስተውለው አልችልም። እባክህን ናና ከጐኔ ተቀመጥ። ኢሳይያስ የጻፈው ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ ሰው?”

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 10

ኢሳይያስ የጻፈው ስለ ኢየሱስ መሆኑን ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው አብራራለት። ደግሞም ፊልጶስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች ሊነግረው ሌሎች የእግዚአብሔር ቃል ክፍሎችን ተጠቀመ።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 11

ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው እንደ ተጓዙ፣ ውሃ ወዳለበት ስፍራ ደረሱ። ኢትዮጵያዊው፣ “እነሆ፣ በዚያ ቦታ ውሃ አለ! ልጠመቅን? አለ። ለነጂውም ሰረገላውን እንዲያቆመው ነገረው።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 12

ስለዚህ ወደ ውሃው ወረዱ፣ ፊልጶስም ኢትዮጵያዊውን አጠመቀው። ከውሃው ከወጡ በኋላ መንፈስ ቅደስ በድንገት ፊልጶስን ወደ ሌላ ስፍራ ነጠቀው፤ ስለ ኢየሱስ ለሰዎች መናገሩንም ቀጠለ።

45. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን — illustration 13

ኢትዮጵያዊው ኢየሱስን በማወቁ እየተደሰተ ወደ አገሩ ለመመለስ ጕዞውን ቀጠለ።

**የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 6፡8-8፡5፤ 8፡26-40።**

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).