44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 1

አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ይሄዱ ነበር። ወደ ቤተ መቅደሱ ደጃፍ እንደ ቀረቡ፣ ገንዘብ ይለምን የነበረ ሽባ ሰው ዐዩ።

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 2

ጴጥሮስ ሽባውን ተመለከተውና፣ “የምሰጥህ ምንም ገንዘብ የለኝም። ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ። በኢየሱስ ስም ተነሣና ተመላለስ!” አለው።

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 3

ወዲያውኑ እግዚአብሔር ሽባውን ሰው ፈወሰው፣ እርሱም መራመድና መዝለል፣ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። በቤተ መቅደሱ አጥር ግቢ የነበሩት ሰዎች ተደነቁ።

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 4

ሕዝብም የተፈወሰውን ሰው ለማየት ፈጥነው ተሰበሰቡ። ጴጥሮስ እንዲህ አላቸው፣ “ይህ ሰው ስለ ተፈወሰ ለምን ተደነቃችሁ? በገዛ ኃይላችን ወይም በጎነታችን አልፈወስነውም። ይልቁንም ይህንን ሰው የፈወሰው የኢየሱስ ኃይልና ኢየሱስ የሚሰጠው እምነት ነው።”

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 5

“ኢየሱስን እንዲገድለው ለሮማው ገዥ የነገራችሁት እናንተ ናችሁ። የሕይወትን ጀማሪ ገደላችሁት፣ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው። ታደርጉት የነበረው ነገር ባይገባችሁም እንኳ፣ መሲሑ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት የተነገሩትን ትንቢቶች ለመፈጸም እግዚአብሔር በድርጊቶቻችሁ ተጠቀመ። ስለዚህ ኃጢአታችሁ ይታጠብላችሁ ዘንድ አሁን ንስሐ ግቡና ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።”

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 6

የቤተ መቅደሱ መሪዎች ጴጥሮስና ዮሐንስ ይናገሩት በነበረው ነገር በጣም ተበሳጩ። ስለዚህ ያዙአቸውና እስር ቤት አስገቡአቸው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች የጴጥሮስን መልእክት አመኑ፣ በኢየሱስ ያመኑት ሰዎች ቊጥርም ወደ 5,000 ገደማ ዐደገ።

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 7

በማግስቱ፣ የአይሁድ መሪዎች ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሊቀ ካህናቱና ወደ ሌሎቹ የሃይማኖት መሪዎች አመጡአቸው። ጴጥሮስንና ዮሐንስን፣ “ይህንን ሽባ ሰው በምን ኃይል ፈወሳችሁት?” ብለው ጠየቁአቸው።

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 8

ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ “ይህ ሰው በመሲሑ በኢየሱስ ኃይል ተፈውሶ በፊታችሁ ቆሞአል። እናንተ ኢየሱስን ሰቀላችሁት፣ እግዚአብሔር ግን እንደ ገና አስነሣው! እናንተ አልተቀበላችሁትም፣ ነገር ግን በኢየሱስ ኃይል ካልሆነ በቀር ሌላ የመዳን መንገድ የለም!”

44. ጴጥሮስና ዮሐንስ ይለምን የነበረውን ሰው ፈወሱ — illustration 9

ጴጥሮስና ዮሐንስ በጣም በድፍረት በመናገራቸው እነዚህ መሪዎች ደነገጡ፣ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ማየት ችለው ነበር። ነገር ግን በዚያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ አስታወሱ። ጴጥሮስንና ዮሐንስን ካስፈራሩአቸው በኋላ፣ እንዲሄዱ ለቀቁአቸው።

**የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 3፡1-4፡22። **

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).