47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 1

ሳውል በሮማ የንጉሠ ነገሥት ግዛት ሁሉ በሚጓዝበት ጊዜ፣ ሮማዊ ስሙን “ጳውሎስ”ን መጠቀም ጀመረ። አንድ ቀን ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች ሊያውጁ ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ ሄዱ። ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ተሰበሰቡበት ከከተማይቱ ውጭ በወንዙ አጠገብ ወዳለ ስፍራ ሄዱ። በዚያ ነጋዴ የነበረች ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት አገኙ። እርስዋ እግዚአብሔርን ትወድና ታመልክ ነበር።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 2

ስለ ኢየሱስ የሚነገረውን መልእክት እንድታምን እግዚአብሔር የልድያን ልብ ከፈተላት፤ እርስዋና ቤተ ሰብዋ ተጠመቁ፣ በቤትዋ እንዲኖሩ ጳውሎስንና ሲላስን ጋበዘቻቸው፣ ስለዚህ እነርሱ ከእርስዋና ከቤተ ሰብዋ ጋር ኖሩ።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 3

ጳውሎስና ሲላስ ብዙ ጊዜ በጸሎት ስፍራ ከሰዎች ጋር ይገናኙ ነበር። በየዕለቱ ወደዚያ ሲሄዱ ጋኔን የያዛት አንዲት ባሪያ ልጃገረድ ትከተላቸው ነበር። እርሷም በዚህ ጋኔን አማካይነት ስለ መጪው ጊዜ ለሰዎች ትተነብይላቸው ነበር፣ ስለዚህ በጥንቈላ ለጌቶችዋ ብዙ ገንዘብ ታስገኝ ነበር።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 4

ባሪያዪቱ ልጃገረድ እነርሱ ሲዘዋወሩ እየተከተለቻቸው፣ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው። የመዳንን መንገድ ይነግሩአችኋል!” በማለት መጮህዋን ቀጠለች። ጳውሎስ እስኪቈጣ ድረስ ይህንን ደጋግማ አደረገች።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 5

በመጨረሻም አንድ ቀን ባሪያዪቱ ልጃገረድ መጮኽ በጀመረች ጊዜ ጳውሎስ ወደ እርስዋ ዘወር አለና በእርስዋ የነበረውን ጋኔን፣ “በኢየሱስ ስም፣ ከእርስዋ ውጣ” አለው። ወዲያውኑ ጋኔኑ ለቀቃት።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 6

የባሪያዪቱ ልጃገረድ ጌቶች የነበሩት ሰዎች በጣም ተቈጡ! ያለ ጋኔኑ ባሪያዪቱ ልጅ ስለ ሰዎች መጪ ጊዜ መናገር እንደማትችል ዐወቁ። ይህም ሰዎች የሚደርስባቸውን ነገር ትነግራቸው ዘንድ ስለማትችል ለጌቶችዋ ገንዘብ አይከፍሉም ማለት ነው።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 7

ስለዚህ የባሪያዪቱ ልጃገረድ ጌቶች ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ሮማ ባለ ሥልጣናት ወሰዱአቸው፣ እነርሱም ደብድበው ወደ እስር ቤት ጣሉአቸው።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 8

እነርሱም ጳውሎስንና ሲላስን በእስር ቤት ውስጠኛ ክፍል አሰሩአቸው እግሮቻቸውን እንኳ ከግንድ ጋር አሰሩአቸው። ሆኖም ግን እከለ ሌሊት ላይ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘመሩ።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 9

በድንገት ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ! የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ ወለል ብለው ተከፈቱ፣ የእስረኞቹ ሁሉ ሰንሰለቶችም ረገፉ።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 10

የእስር ቤቱ ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቃ፣ የእስር ቤቱ በሮች ሁሉ መከፈታቸውን ባየ ጊዜ ፈራ! እስረኞቹ ሁሉ ያመለጡ መሰለው፣ ስለዚህ ራሱን ለመግደል ዐሰበ። (እስረኞቹ እንዲያመልጡ ካደረገ የሮማ ባለ ሥልጣናት እንደሚገድሉት ዐወቀ።) ነገር ግን ጳውሎስ ዐየውና፣ “ተው! ራስህን አትጕዳ። ሁላችንም እዚህ አለን” ብሎ ጮኸበት።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 11

የእስር ቤቱ ጠባቂ ወደ ጳውሎስና ሲላስ እየመጣ እያለ ተንቀጠቀጠና፣ “እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀ። ጳውሎስ፣ “በጌታ በኢየሱስ እመን፣ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” ብሎ መለሰለት። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤቱ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው። ጳውሎስ በቤቱ ለነበሩት ሁሉ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች ሰበከላቸው።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 12

የእስር ቤት ጠባቂውና መላው ቤተ ሰቡ በኢየሱስ አምነው ተጠመቁ። ከዚያም የእስር ቤት ጠባቂው ለጳውሎስና ለሲላስ ምግብ አቀረበላቸውና በአንድነት ደስ አላቸው፡

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 13

በማግስቱ የፊልጵስዩስ መሪዎች ጳውሎስና ሲላስን ከእስር ቤት ፈቱአቸውና ከፊልጵስዩስ እንዲሄዱ ጠየቁአቸው። ጳውሎስና ሲላስ ልድያንና አንዳንድ ሌሎች ወዳጆችን ጐበኙና ከተማይቱን ለቀው ሄዱ። ስለ ኢየሱስ የሚናገረው የምሥራች መስፋፋቱን ቀጠለ ቤተ ክርስቲያንም ማደግዋን ቀጠለች።

47. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ — illustration 14

ጳውሎስና ሌሎች ክርስቲያን መሪዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች እየሰበኩና እያስተማሩ ወደ ብዙ ከተሞች ተጓዙ። ደግሞም በአብያተ ክርስቲያናቱ ላሉ አማኞች ሊያበረታቱአቸውና ሊያስተምሩአቸው ብዙ መልእክቶችን ጻፉላቸው። ከእነዚህ መልእክቶች አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉት መጻሕፍት ሆኑ።

**የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሐዋርያት ሥራ 16፡11-40።**

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).