48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 1

እግዚአብሔር ዓለምን በፈጠረ ጊዜ ሁሉም ነገር ፍጹም ነበረ። ኃጢአት አልነበረም። አዳምና ሔዋን እርስ በርሳቸው ይዋደዱ ነበር፣ እግዚአብሔርንም ይወዱት ነበር። በሽታ ወይም ሞት አልነበረም። እግዚአብሔር ዓለም እንድትሆን የፈለገው እንደዚህ ነበር።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 2

ሰይጣን በገነት ሔዋንን ያስት ዘንድ በእባቡ በኩል ተናገረ። ከዚያ በኋላ እርስዋና አዳም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። እነርሱ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት በምድር ያለ ሰው ሁሉ ይታመማል ይሞታልም።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 3

አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ከዚያም የበለጠ መጥፎ ነገር እንኳ ሆነ። እነርሱ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆኑ። ከዚህ የተነሣ ከዚያን ጊዜ አነሥቶ ሁሉም ሰው በኃጢአት ባሕርይ ተወልዶአል ደግሞም የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል የነበረው ግንኙነት በኃጢአት ተቋረጠ። ነገር ግን እግዚአብሔር ያንን ግንኙነት የመመለስ ዕቅድ ነበረው።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 4

ከሔዋን ዝርያዎች አንዱ የሰይጣንን ራስ እንደሚቀጠቅጥ፣ ሰይጣንም ሰኰናውን እንዲያቈስል እግዚአብሔር ተስፋ ሰጠ። ይህም ሰይጣን መሲሑን ይገድላል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ገና ያስነሣዋል ማለት ነው፣ ከዚያም መሲሑ የሰይጣንን ኃይል ለዘላለም ይቀጠቅጠዋል። ከብዙ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር መሲሑ ኢየሱስ መሆኑን ገለጠ።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 5

እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ በጥፋት ውሃ ባጠፋ ጊዜ፣ በእርሱ ያመኑትን ሰዎች ለማዳን መርከብ አቀረበ። በተመሳሳይ መንገድ ሰው ሁሉ በኃጢአቱ ምክንያት መጥፋት ይገባው ነበር፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ለማዳን ኢየሱስን ሰጠ።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 6

ለብዙ መቶ ዓመታት ካህናት ለኃጢአታቸው የሚገባቸውን ቅጣት ለማሳየት ስለ ሕዝቡ ያለ ማቋረጥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ነገር ግን እነዚያ መሥዋዕቶች ኃጢአታቸውን ሊያስወግዱ አልቻሉም። ኢየሱስ ታላቁ ሊቀ ካህናት ነው። ከሌሎች ካህናት በተለየ ሁኔታ ራሱን በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ኃጢአት ማስወገድ የሚችል ብቸኛ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ኢየሱስ ማንኛውም ሰው የሠራውን የእያንዳንዱን ኃጢአት ቅጣት ስለ ወሰደ ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 7

እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ “የምድር ሕዝብ ወገኖች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” ብሎ ነገረው። ኢየሱስ ከአብርሃም ትውልድ ነው። በእርሱ በኩል የሕዝብ ወገኖች ሁሉ ተባርከዋል፣ ምክንያቱም በኢየሱስ የሚያምን እያንዳንዱ ሰው ከኃጢአት ድኖአል፣ እንዲሁም የአብርሃም መንፈሳዊ ትውልድ ይሆናል።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 8

ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ እግዚአብሔር ለአብርሃም በነገረው ጊዜ፣ እግዚአብሔር በልጁ በይስሐቅ ፈንታ የመሥዋዕት በግ አቀረበ። ሁላችንም በኃጢአታችን መሞት ይገባናል! ነገር ግን እግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ በእኛ ቦታ እንዲሞት የእግዚአብሔር በግ የሆነውን ኢየሱስን ሰጠ።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 9

እግዚአብሔር በግብፅ ላይ የመጨረሻውን መቅሠፍት በላከ ጊዜ እንከን የሌለበት ጥቦት እንዲያርዱና ደሙን በበሩ መቃንና ጉበን ላይ እንዲረጩት ለእስራኤላውያን ቤተ ሰቦች ተናገረ። እግዚአብሔር ደሙን ባየ ጊዜ ቤቶቹን አልፎ ሄደ በኵር ልጆቻቸውንም አልገደለም። ይህ ታሪካዊ ድርጊት ፋሲካ ተብሎአል።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 10

ኢየሱስ የፋሲካ በጋችን ነው። እርሱ ፍጹምና ያለ ኃጢአት ነው በፋሲካ በዓል ጊዜም ተገደለ። ማንኛውም ሰው በኢየሱስ በሚያምንበት ጊዜ፣ የኢየሱስ ደም ለዚያ ሰው ኃጢአት ክፍያ ነው፣ የእግዚአብሔር ቅጣትም በዚያ ሰው ላይ ያልፋል።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 11

እግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቡ ከነበሩት ከእስራኤላውያን ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ነገር ግን አሁን እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው የሚሆን ዐዲስ ቃል ኪዳን አድርጎአል። በዚህ ዐዲስ ቃል ኪዳን ምክንያት ከማንም ሕዝብ ወገን የሆነ ማንኛውም ሰው በኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን መሆን ይችላል።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 12

ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ያወጀ ታላቅ ነቢይ ነበረ። ኢየሱስ ግን ከሁሉም የላቀ ነቢይ ነው። እርሱ አምላክ ነው፣ ስለዚህ እርሱ ያደረገውና የተናገረው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ሥራና ቃል ነው። ስለዚህ ነው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ተብሎ የሚጠራው።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 13

ከዝርያዎቹ አንዱ ንጉሥ ሆኖ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ለዘላለም እንደሚገዛ እግዚአብሔር ለንጉሥ ዳዊት ተስፋ ሰጠው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና መሲሑ ስለሆነ፣ ለዘላለም መግዛት የሚችል ያ ልዩ የዳዊት ዘር ነው።

48. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሲሕ ነው — illustration 14

ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ነበር፣ ኢየሱስ ግን የፍጥረት ዓለም ሁሉ ንጉሥ ነው! ተመልሶ ይመጣና በፍትሕና በሰላም መንግሥቱን ለዘላለም ይገዛል።

**የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከዘፍጥረት 1-3፤ 6፤ 14፤ 22፤ ዘጸአት 12፣ 20፤ 2ኛ ሳሙኤል 7፤ ዕብራውያን 3፡1-6፤ 4፡14-5፡10፤ 7፡1-8፡13፤ 9፡11-10፡18፤ ራእይ 21።**

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).