2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 1

አዳምና ሚስቱ እግዚአብሔር በሠራላቸው የአትክልት ስፍራ ሲኖሩ በጣም ደስተኞች ነበሩ። ሁለቱም ራቁታቸውን ነበሩ ይሁን እንጂ ራቁታቸውን መሆናቸው እንዲተፋፈሩ አላደረጋቸውም፤ ምክንያቱም ኃጢአት በዓለም አልነበረም። እነርሱም በአትክልቱ ስፍራ እየተመላለሱ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገሩ ነበር።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 2

ነገር ግን ተንኮለኛ እባብ በአትክልቱ ውስጥ ነበር። ሴትየዋንም ጠየቃት “እግዚአብሔር በእርግጥ በአትክልቱ ውስጥ ካለው ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ ብሎችኋልን?” አላት።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 3

ሴቲቱም፣ “እግዚአብሔር ክፉንና መልካሙን ከሚያሳውቀው የእውቀት ዛፍ በስተቀር ከማንኛውም የዛፍ ፍሬ መብላት እንደምንችል ተናግሮናል። ነገር ግን ያንን ፍሬ ብትበሉ ወይም ብትነኩት እንኳ ትሞታላችሁ” አለን።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 4

እባቡም ለሴቲቱ መልሶ፣ “ይህ እውነት አይደለም አትሞቱም ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዓይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ እንደ እግዚአብሔርእንደምትሆኑ እግዚአብሔርስለሚያውቅ ነው አትብሉት ያላችሁ” አለ።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 5

ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዓይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ ከፍሬው ወስዳ በላች። ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏም ሰጠችው። እርሱም ከዛፉ ፍሬ በላ።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 6

ወዲያውም የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ። ራቁታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ፤ ቅጠልም እንደ ልብስ ሰፍተው ገላቸውን ለመሸፈን ሞከሩ።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 7

ሰውዬውና ሚስቱም የእግዚአብሔር ድምፅ በአትክልቱ መካከል ሲመላለስ ሰምተው ሁሉም ከእግዚአብሔር ፊት ተሸሸጉ። እግዚአብሔርም አዳምን ጠርቶ “የት ነህ?” አለው። አዳምም “በአትክልቱ ስፍራ ስትመላለስ ሰማሁ ራቁቴን ስለ ሆንኩ ፈራሁ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 8

እግዚአብሔርም “ራቁትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ከርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው። አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለው። እግዚአብሔር ሴቲቱንም ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?" አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 9

እግዚአብሔር እባቡን እንዲህ አለው፤ “የተረገምህ ነህ፣ በደረትህ ትሳባለህ አፈርም ትበላለህ አንተና ሴቲቱ ጥለኞች ትሆናላችሁ የአንተ ልጆችና የእርሷም ልጆች እንዲሁ ጥለኞች ይሆናሉ የሴቲቱ ዘር ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።”

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 10

እግዚአብሔር ሴቲቱንም አላት “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፣ ፍላጎትሽ ወደ ባልሽ ይሆናል እርሱም የበላይሽ ይሆናል።”

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 11

እግዚአብሔርም አዳምን እንዲህ አለው። “የሚስትህን ቃል ሰምተህ አትብላ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ ፍሬ በልተሃልና ምድር ካንተ የተነሣ ተረግማለች። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ። ከዚያም ትሞታለህ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ።” አዳምም ሚስቱን የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሔዋን ብሎ ጠራት ትርጓሜውም ሕይወት ሰጪ ማለት ነው፤ እግዚአብሔርም ከእንስሳ ቆዳ አዘጋጅቶ አዳምንና ሔዋንን አለበሳቸው።

2. ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ — illustration 12

እግዚአብሔርም ሰው መልካምንና ክፉን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ቀጥፎ እንዳይበላና ለዘላለምም እንዳይኖር አዳምና ሔዋንን ከውቡ የአትክልት ስፍራ አስወጣቸው። ከዚያም ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅና ማንም ከዚህ የሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ ኃይለኞች መላእክትን በአትክልቱ ስፍራ አኖረ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ዘፍጥረት 3

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).