33. የአርሶ አደሩ ታሪክ

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 1

አንድ ቀን ኢየሱስ በሐይቁ ዳርቻ አጠገብ በጣም ብዙ ሕዝብ እያስተማረ ነበር። ኢየሱስ ሊናገራቸው በቂ ቦታ ለማግኘት በውሃው ዳርቻ በጀልባ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ በጣም ብዙ ሰዎች ሊሰሙት መጡ። በጀልባው ተቀመጠና ሕዝቡን አስተማረ።

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 2

ኢየሱስ ይህንን ታሪክ ተናገረ። “አንድ አርሶ አደር ዘር ሊዘራ ወጣ። በእጁ ዘሩን ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፣ ወፎችም መጥተው ያን ዘር በሙሉ በሉት።”

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 3

“ሌላው ዘር ብዙ መሬት በሌለበት በአለታማ መሬት ላይ ወደቀ፣ ነገር ግን ሥሩ ወደ መሬት መጥለቅ አልቻለም። ፀሐይዋ በወጣችና በሞቀች ጊዜ፣ ቡቃያው ጠወለገና ደረቀ።”

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 4

“አሁንም ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ። ይህ ዘር መብቀል ጀመረ፣ ነገር ግን እሾኹ አነቀው። ስለዚህ በእሾኻማው መሬት ላይ የበቀለው ቡቃያ ምንም ፍሬ አላፈራም።”

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 5

“ሌላው ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ። ይህ ዘር በቀለና አንዱ 30፣ አንዱ 60፣ አንዱም መቶ ፍሬ ሰጠ። ጆሮ ያለው ይስማ!”

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 6

ይህ ታሪክ ደቀ መዛሙርቱን ግራ አጋባቸው። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ አብራራላቸው፣ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። የመንገዱ ዳር የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ሰው ነው፣ ነገር ግን አያስተውለውም፣ ዲያብሎስም ቃሉን ይወስድበታል።”

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 7

“በአለታማ መሬት የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በደስታ የሚቀበለው ሰው ነው። ነገር ግን መከራ ወይም ስደት በሚያጋጥመው ጊዜ እምነቱን ይተዋል።”

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 8

“እሾኻማው መሬት የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ሰው ነው፣ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የዚህ ዓለም ዐሳብ፣ ባለጠግነትና ደስታ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ያንቃል። ከዚህ የተነሣ፣ የሰማው ትምህርት ፍሬ አያፈራም።

33. የአርሶ አደሩ ታሪክ — illustration 9

“መልካሙ መሬት ግን የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፣ የሚያምነውና ፍሬ የሚያፈራ ሰው ነው።”

**የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 13፡1-8፣ 18-23፤ ማርቆስ 4፡1-8፣ 13-20፤ ሉቃስ 8፡4-15።**

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).