35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 1

አንድ ቀን ኢየሱስ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችንና ሊሰሙት የተሰበሰቡ ሌሎች ኃጢአተኞችን ያስተምር ነበር።

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 2

ደግሞም በዚያ የነበሩ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ወዳጆች አድርጎ ሲቀበላቸው ዐዩ፣ እርስ በርሳቸውም ይነቅፉት ጀመር። ስለዚህ ኢየሱስ ይህንን ታሪክ ነገራቸው።

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 3

ሁለት ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበር። ታናሹ ልጅ አባቱን፣ አባቴ ሆይ፣ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል አሁን ስጠኝ!’ አለው። ስለዚህ አባትዬው ገንዘቡን ለሁለቱ ልጆቹ አካፈላቸው።"

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 4

“ታናሹ ልጅ ወዲያውኑ ያለውን ሁሉ ሰበሰበና ሩቅ አገር ሄዶ በኃጢአት እየኖረ ገንዘቡን አጠፋ።

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 5

“ከዚያ በኋላ ታናሹ ልጅ በነበረበት አገር ጽኑ ረሀብ ሆነ፣ ምግብ የሚገዛበት ገንዘብም አልነበረውም። ስለዚህ ብቸኛ የነበረውን፣ እሪያዎችን የመመገብ ሥራ ያዘ። በጣም ተጐሳቊሎና ተርቦ ስለ ነበር የእሪያዎችን ምግብ ለመብላት ይመኝ ነበር።”

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 6

“በመጨረሻ፣ ታናሹ ልጅ ለራሱ እንዲህ አለ፣ ‘ምን እያደረግሁ ነው? የአባቴ አገልጋዮች ሁሉ የሚበሉት ብዙ ምግብ አላቸው፣ እኔ ግን ተርቤአለሁ። ወደ አባቴ ተመልሾ እሄድና ከአገልጋዮቹ አንዱ እንዲያደርገኝ እለምነዋለሁ።’”

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 7

ስለዚህ ታናሹ ልጅ ወደ አባቱ ቤት መመለስ ጀመረ። ገና በሩቅ እያለ አባቱ ዐየውና አዘነለት። ወደ ልጁ ሮጠና አቀፈው ሳመውም።"

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 8

“ልጁም አለ፣ ‘አባቴ ሆይ፣ እግዚአብሔርንና አንተን በድዬአለሁ። ልጅህ ልባል አይገባም።’”

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 9

“ነገር ግን አባቱ ከአገልጋዮቹ ለአንዱ እንዲህ ብሎ ነገረው፣ ‘ፈጥነህ ሂድና ማለፊያ ልብስ አምጥተህ ለልጄ አልብሰው! ለጣቱ ቀለበት ለእግሩም ጫማ አድርግለት። ከዚያም እንበላና ደስ ይለን ዘንድ የሰባ ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱ፣ ምክንያቱም ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፣ ሕያውም ሆኖአል! ጠፍቶ ነበር፣ አሁን ግን ተገኝቶአል!’”

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 10

“ስለዚህ ሰዎቹ ደስ ይላቸው ጀመር። ብዙ ሳይቆይ፣ ይሠራበት ከነበረው እርሻ ታላቅ ወንድሙ ወደ ቤት መጣ። የሙዚቃና የዘፈን ድምፅ ሰማ፣ ምን እየሆነ ነው ብሎም ተገረመ።”

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 11

“ታላቁ ልጅ ወንድሙ ስለ መጣ እየተደሰቱ መሆናቸውን ባወቀ ጊዜ፣ በጣም ስለ ተቈጣ ወደ ቤት ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም። አባቱ ወጣና ገብቶ ከእነርሱ ጋር እንዲደሰት ለመነው፣ እርሱ ግን እምቢ አለ።”

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 12

ታላቁ ልጅ አባቱን እንዲህ አለው፣ ‘በእነዚህ ዓመታት ሁሉ በታማኝነት ለአንተ ሠርቼአለሁ! ከቶ ትእዛዝህን አልተላለፍኩም፣ እስካሁንም ከጓደኞቼ ጋር እንድደሰት አንድ ጥቦት ፍየል እንኳ አልሰጠኸኝም። ኃጢአት በመሥራት ገንዘብህን ያጠፋው ይህ ልጅህ ግን ወደ ቤት በመጣ ጊዜ፣ የሰባ ፍሪዳ አረድህለት!"

35. የርኅሩኁ አባት ታሪክ — illustration 13

“አባቱ እንዲህ ብሎ መለሰለት፣ ‘ልጄ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ ያለኝም ነገር ሁሉ የአንተ ነው። መደሰታችን ግን ትክክል ነው፣ ምክንያቱም ወንድምህ ሞቶ ነበር፣ አሁን ግን ሕያው ሆኖአል። ጠፍቶ ነበር፣ አሁን ግን ተገኝቶአል!”

**የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከሉቃስ 15፡11-32።**

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).