38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 1

አይሁድ በያመቱ የፋሲካን በዓል ያከብሩ ነበር። ይህም በዓል ከብዙ ምእት ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ቅድማያቶቻቸውን በግብፅ ከነበረው ባርነት እንዴት እንዳዳናቸው የሚከበር ነበር። ኢየሱስ መጀመሪያ በይፋ መስበኩንና ማስተማሩን ከጀመረ ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ፣ ይህን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋር ሊያከብር እንደ ፈለገ፣ በዚያም እንደሚገደል ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 2

ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ይሁዳ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር። ይሁዳ የሐዋርያቱ የገንዘብ ከረጢት ኃላፊ ነበር፣ ነገር ግን ገንዘብ ይወድ ነበርና ብዙ ጊዜ ከከረጢቱ ውስጥ ገንዘብ ይሰርቅ ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሱ በኋላ፣ ይሁዳ ወደ አይሁድ መሪዎች ሄደና ኢየሱስን በገንዘብ አሳልፎ ሊሰጣቸው ተስማማ። ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የአይሁድ መሪዎች እንደ ካዱና ሊገድሉት ያሤሩ እንደ ነበር ዐወቀ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 3

የአይሁድ መሪዎች በሊቀ ካህናቱ እየተመሩ፣ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ለይሁዳ ሠላሳ ብር ከፈሉት። ልክ ነቢያት እንደ ተነበዩት ይህ ሆነ። ይሁዳ ተስማማ፣ ገንዘቡንም ይዞ ሄደ። ኢየሱስን እንዲይዙት ሊረዳቸው አጋጣሚ መፈለግ ጀመረ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 4

በኢየሩሳሌም፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ፋሲካን አከበረ። በፋሲካው ምግብ ጊዜ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ቈረሰ። እንዲህም አለ፣ “እንካችሁ ይህንን ብሉ። ይህ ስለ እናንተ የተሰጠ ሥጋዬ ነው። ይህንን ለመታሰቢያዬ አድርጉት።” በዚህ ዓይነት ኢየሱስ ሥጋው ስለ እርሱ እንደሚሠዋ ነገራቸው።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 5

ከዚያም ኢየሱስ ጽዋን አንሣና፣ “ይህንን ጠጡ። ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የዐዲስ ኪዳን ደሜ ነው። ይህንን በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 6

ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ደነገጡ፣ እንዲህ ያለ ነገር ማን ያደርጋል ብለውም ጠየቁ። ኢየሱስ፣ “ይህንን ቊራሽ እንጀራ የምሰጠው ሰው እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። ከዚያ በኋላ እንጀራውን ለይሁዳ ሰጠው።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 7

ይሁዳ እንጀራውን ከተቀበለ በኋላ፣ ሰይጣን ገባበት። ይሁዳ ኢየሱስን እንዲይዙ የአይሁድ መሪዎችን ሊረዳቸው ሄደ። ጊዜው ማታ ነበር።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 8

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እራት ከበሉ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ሄዱ። ኢየሱስ፣ “ዛሬ ማታ ሁላችሁም ትተዉኛላችሁ። ‘እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ሁሉ ይበተናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል” አለ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 9

ጴጥሮስ፣ “ሌሎቹ ሁሉ ቢተዉህ እንኳ፣ እኔ ግን አላደርገውም!” ብሎ መለሰ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፣ “ሰይጣን ሁላችሁንም ሊወስዳችሁ ይፈልጋል፣ ነገር ግን ጴጥሮስ እምነትህ እንዳይደክም ጸልዬልሃለሁ። እንደዚያም ሆኖ ግን ዛሬ ማታ ዶሮ ከመጮኹ በፊት እንደማታውቀኝ እንኳ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ።”

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 10

በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስ፣ “መሞት ቢኖርብኝ እንኳ፣ ከቶ አልክድህም” አለው። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ይህንኑ አሉ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 11

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ቦታ ሄደ። ኢየሱስ ወደ ፈተና እንዳይገቡ እንዲጸልዩ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። ከዚያም ኢየሱስ ብቻውን ሊጸልይ ሄደ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 12

ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ጸለየ፣ “አባቴ ሆይ፣ ቢቻልስ ይህን የመከራ ጽዋ እንዳልጠጣው አድርግ። ነገር ግን የሰዎች ኃጢአት ይቅር የሚባልበት ሌላ መንገድ ከሌለ፣ ፈቃድህ ይሁን።” ኢየሱስ በጣም ታወከ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። እግዚአብሔር ሊያበረታታው መልአክ ላከ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 13

ከእያንዳንዱ የጸሎት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመላለሰ፣ እነርሱ ግን ተኝተው ነበር። ሦስተኛ በተመለሰ ጊዜ ግን፣ “ተነሡ! አሳልፎ የሚሰጠኝ እዚህ ነው” አለ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 14

ይሁዳ ከአይሁድ መሪዎች፣ ከወታደሮችና ከብዙ ሕዝብ ጋር መጣ። ሰይፍና ዱላ ይዘው ነበር። ይሁዳ ወደ ኢየሱስ መጣና፣ “መምህር ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” አለው፣ ሳመውም። ይህም የአይሁድ መሪዎች ማንን እንደሚይዙ ምልክት ነበር። ከዚያም ኢየሱስ፣ “ይሁዳ፣ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠኛለህን?” አለ።

38. ኢየሱስ ተላልፎ ተሰጠ — illustration 15

ወታደሮቹ ኢየሱስን እንደ ያዙት፣ ጴጥሮስ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ። ኢየሱስ፣ “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ! ይከላከሉልኝ ዘንድ የመላእክት ሠራዊት እንዲልክልኝ አባቴን መጠየቅ እችላለሁ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ የሰውዬውን ጆሮ ፈወሰው። ኢየሱስ ከተያዘ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ሸሹ።

**የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፡- ከማቴዎስ 26፡14-56፤ ማርቆስ 14፡10-50፤ ሉቃስ 22፡1-53፤ ዮሐንስ 12፡6፤ 18፡1-11።**

Read in the reader

Free to use, adapt, and share under an open license (CC BY-SA 4.0).